ወተት ሊገዛ የወጣ ልጅ በድንገት መሃል ግንባሩን በአልሞ ተኳሾች ይመታና ይወድቃል። ግማሹ ይሸሻል። አላስችል ያለው ርዳታ ለመስጠት ይሞክራል። በመካከል እናት የልጇን መውደቅ ትሰማለች። ጨርቋን ጥላ እያለቀሰች አስፋልት መሃል ተዘርሮ የወደቀው ልጇ ላይ ተጠመጠመች። በደም ተጨማልቃ እያነባች ህይወቱን ለመመለስ ፈለገች። ልጅ መሃል ግንባሩን ተወግቶ ነበርና ሕይወቱ አልፋለች። እናት አበደች። “እኔን፣ እኔ ልደፋ … …” አነባች። አስከሬኑን ለመውሰድ ሚኒሊክ ሆስፒታል ተሰለፈች።
ብዙዎች በተመሳሳይ አንብተዋል። በርካታ እስካሁንም እያነቡ ያሉ አሉ። ይህ የሆነው 1997 ዓም የህዝብ ድምጽ ከተሰረቀ በኋላ ህዝብ ለምን ድምጼ ተሰረቀ ብሎ ስለጠየቀ ነው። በገዳዮቹና ባስገዳዮቹ ዘንድ ይህ ልጅ “ጸረ ሰላም ኃይል” ነው። ይህንን አጭር መልዕክት ያስታወሱን አንድ የራስ ደስታ ሆስፒታል ሠራተኛ ናቸው።
“ተወደደም ተጠላም ኢትዮጵያ ተሳክራለች። ሆዷ ነፍሯል” ሲሉ አስተያየታቸውን የሚሰጡ እንደሚሉት፣ በየቦታው ብሶት መርቅዞ ገደቡን አልፏል። የከፋቸው ብሶታቸውን ታግሰው የሚይዙበት አቅም እያጡ ነው። ገዢዎችም ደምን በደም ላይ፣ ግፍን በግፍ ላይ፣ ቁርሾን በቁርሾ ላይ እያደራረቡ ኢትዮጰያን እያነፈሯት ነው። ቆም ብሎ የሚያስብ አልተገኘም። የተመቻቸው ይገነባሉ። ያስመጣሉ፤ ይልካሉ። ይሸቅጣሉ፤ ያሻቅጣሉ። በውጪ አገር ባንኮች ያከማቻሉ። ይህ ተግባራቸው ስለሚያስጨንቃቸው እርቅ፣ ሰላማዊ ሽግግር፣ ምርጫና ሹም ሽር ያሳስባቸዋል። ይፈሩታል፣ አይወዱትም!! የከፋቸው ሰልችቷቸዋል። ስሜታቸውን የሚቆጣጠሩበት ልጓም አጥተዋል። ርህራሄያቸው እያለቀ ነው። ሃዘኔታቸው ተንጠፍጥፏል። እልህና ቁጭት ሊነዳቸው ዳር ደርሰዋል። አማራ፣ ደቡብ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ … በየቦታው የሚታየውና የሚሰማው መልካም ዜና አይደለም። ይህ የማይገባቸው ለተውሰኑት ብቻ መሆኑ ደግሞ ያሳስበናል።
እነዚህ ክፍሎች ማንኛውም የህዝብ ጥያቄ ስለሚያስበረግጋቸው ምላሻቸው ጥይት፣ ኃይል፣ እስር፣ ማሰቃየት (ቶርቸር)፣ መግደል፣ ማሸማቀቅ፣ አሸባሪ በማለት መፈረጅ፣ ፈርጆ ወኅኒ ማጎር … … ብቻ እንደሆን ስምምነት አለ። ይህንን ተግባር የሚደገፉ ጥቂት ተጠቃሚዎች ድፍን ህዝብ ሲያለቅስና ሲያዝን በድል አድራጊነት ስሜት ይጥለቀለቃሉ። ያሽካካሉ። በፈለጉት አይነት አልኮል ይራጫሉ፤ ቺርስ ይባባላሉ። ጊዜውንና ውጥረቱን ከማስተዋል ይልቅ “ጦርነትን እንሰራዋለን” በሚል የነተበ ስሜት ውስጥ እየደነሱ፣ “እየገደልን ፵ ዓመት እንመራለን” በማለት መሳሪያ እየወለወሉ ቃላችውን ያድሳሉ። ቃላቸውን የሚያድሱት ደግሞ ህዝብ በተነፈሰ ቁጥር ደም በማፍሰስ፣ አካል በማጉደል፣ በማሰር፣ በመሰወር ፣ በሌላም በሌላም!!
ሰሞኑን እየሆነ ያለው ከላይ የተገለጸው የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሃት) የተለመደ ባህሪ እንጂ አዲስ ጉዳይ እንዳልሆነ በተለያየ መልኩ እየተገለጸ ነው። በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን የመብት ጥያቄ ተከተሎ የተሰጠውና እየተሰጠ ያለው ምላሽ ምሬትንና ቂምን፣ በደልንና በቀልን የሚያጠናክር ከመሆን የዘለለ ውጤት እንደማያመጣ ለጎልጉል አስተያየት የሰጡ ገልጸዋል። በደሉ አይሎ ካድሬውና የፖሊስ ኃይል ህዝብን እየተቀላቀለ መሆኑንን የሚናገሩት የጨሊያ ነዋሪ፣ የምናውቃቸው የኦህዴድ የበታች አመራሮች፣ ታጣቂዎች፣ የፖሊስ ሃይሎች ሀዝብን እየተቀላቀሉ ሲሊ አመልክተዋል። በወረዳና በዞን ያሉ ውስን አመራሮች በወንጀልና በሙስና ስለተጨማለቁ በፍርሃቻ ህወሃትን ቢያገለግሉም በዚህ አቋማቸው ይዘልቃሉ ተብሎ እንደማይገመት ጠቁመዋል።
“ተቆጣጥረነዋል”
አሁን ኢትዮጵያን የገጠማት ችግር ጨለማው እየበረታ መሆኑን እንደሚያመላክት ብዙዎች ይናገራሉ። ችጋር፣ ድህነት፣ ስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ያደቀቃቸው ወገኖች ምሬታቸው የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱንና እየከሰመ ቢነሳም፣ በየአቅጣጫው የሚሰማው የህዝብ የተቃውሞ ድምጽ መበርከት የጨለማውን መጠንከር ነጸብራቅ እንደሆነ እምነት አለ። አመጹን “ተቆጣጥረነዋል” የሚሉት ነፍጥ አንጋቢዎችና መሪዎቻቸውም ይህንኑ እያመኑ ነው።
በኦሮሚያ ክልል ህዝብ ያነሳውን ጥያቄና መብትን የማስከበር ሰላማዊ ትግል “አንዳንድ ሁከት” አድራጊዎች የጀመሩት ነው ይሉታል። በነካ አፋቸው ደግሞ የጦር መሳሪያ የታጠቁና ማረሚያ ቤት በመስበር እስረኞችን ለማስመለጥ የተደረገ ሙከራ ስለመኖሩ ይናገራሉ። በትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (በህወሃት) ተሰርቶ ኦሮሚያን በውክልና የሚመራው የኦህዴድ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ፈቃዱ ተሰማ በኩል የተላለፈው መግለጫ ፋብሪካዎችን የማቃጠልና ንቅናቄውን የተቃወሙ “ንጹሃን”ን የማጥቃት ሙከራ እንደነበር ያወሳል። በዚሁ እርስ በእርስ በሚጣረስ መግለጫ፣ የቢሮው ኃላፊ “የሁከቱ መነሻ የሆነው ኦነግና ግንቦት ሰባትን ጨምሮ በሃገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፅንፈኛ አካላት ሁለቱን አብሮ የመልማት ሃሳብን ያነገቡ እቅዶችን አስመልክቶ ሃሰተኛ ፕሮፖጋንዳ በማስተላለፍ እና የክልሉን ነዋሪዎች እነርሱ ለሚያስቡት ተልዕኮ ማስፈጸሚያነት በማዋል፤ ትምህርት ተቋማት ዘንድ በተቃውሞ መልክ ይስተዋሉ የነበሩ ብጥብጦችም እያደጉ መጥተውና ከዩኒቨርሲቲዎችም ወጥተው በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ላይ መታየት ጀምረዋል …” በማለት “አንዳንድ ሁከት” ያሉትን ህዝባዊ ሰላማዊ ተቃውሞ ያብራሩታል። ሲያጠቃልሉም “ተቆጣጥረነዋል” ብለዋል።
ኃላፊው ይህን ቢሉም በተግባር የሚታየው ግን የተማሪዎቹን ጥያቄ ህዝብ ተቀብሎት ሰፍቷል። ከተሞችን እስከ መቆጣጠር ደርሷል። ሚሊሻዎችና የፖሊስ ሃይላት፣ የበታች ካድሬዎችና ጠርናፊዎች ሰላማዊውን ተቃውሞ ስለመቀላቀላቸው ይፋ እየሆነ ነው። የ“ተሰውትን ባለራዕይ” የመለስን ፕሮጀክት ማቃጥልና አወላልቆ መጣል ላይ ተደርሷል። ሰላማዊው ተቃውሞ ባለፉት ሶስት ሳምንታት እየጠነከረ መምጣቱን ማቆም ባለመቻሉ ንቅናቄውን ያስነሳው የማስተር ፕላን አጀንዳ ለጊዜው መቆሙ ይፋ ተደርጓል። በማዕከል፣ በክልል፣ በታጣቂ ሃይላት አመራሮች ዘንድ እርስ በእርሱ ሲጣረስ የነበረው መግለጫም እልባት ማግኘት ችሏል። ግን የረፈደበት ነው። ሕዝባዊ ንቅናቄ ለሳምንታት መዝለቅ መቻሉና በመጠኑ ደግሞ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እያካተተ እያደገ መምጣቱ በጣም እየረፈደ ለመምጣቱ በቂ ማመላከቻ ነው፡፡
ጅብ ካመለጠ ውሻ ጮኸ
በውዝግብ የካድሬውን ይሁንታ ሳያገኙ በሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲና የሳቸው ወዳጆች በሆኑ የህወሃት ቁንጮዎች አማካይነት ኦሮሚያን የመምራት እድል ያገኙት ሙክታር የሰጡት መግለጫ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” እንዲሉ ሆኗል። የአባ ዱላ ምክትል ሆነው ክልሉን ሲመሩ ባደረጉት የግልበጣ ሙከራ ተሽቀንጥረው የነበሩትና “ባለጸጋ” የሚባሉት ሙክታር ከድር ዳግም ኦሮሚያን የመምራት እድል ያገኙት “ለባለሃብቱ ባበረከቱት ውለታ ነው” ሲሉ የቅርብ ጓደኞቻቸው ይመሰክራሉ። ከመሬት ጋር በተያያዘ ከጅማ ጀምሮ የሚታሙት ሙከታር ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ “በማስተር ፕላኑ ላይ ከሕዝብ ጋር መግባባት ካልተደረሰ በቀር ተግባራዊ አይሆንም” በማለት ማስተር ፐላኑን ከህዝብ ጋር የማስተዋወቅ ስራ በወጉ አለመሰራቱን በድክመት አስቀምጠዋል። በዚሁ ድካም ሳቢያ ስለተገደሉ ወገኖች ያሉት ነገር የለም። ህዝብ በእምቢታ ያስቆመውን ጉዳይ እሳቸው እንደ መልካም አስተዳዳሪ “አንተ የማትፈልገው ከሆነ አስቆምልሃለሁ” ማለታቸውን “ተራ ማዘናጊያ” ሲሉ ያጣጣሉት ጥቂት አይደሉም።
“እንደ መሪ ከመታዘዝ ውጪ አቋም የመውሰድ ችግር ቢኖርባቸውም ለአፋቸው እንኳን ስለደረሰው ሰብዓዊ ቀውስ ጥቂት ቢሉ በተሻለ ነበር” ሲሉ ያናናቋቸው በርካታ ናችው። ሰላማዊ ጥያቄ በማንሳታቸው ስለተገደሉ፣ አካላቸው ስለጎደለ፣ ስለታስሩና ስለተሰወሩ ዜጎች ለቀረበው ጥያቄ መልስ አለመሰጠቱ አሁንም ተቃውሞው ለመቆሙ ዋስትና እንደማይሆን ከግምት የዘለለ እምነት አለ።
ጨለማው እንዳይውጠን – እንዳይውጣችሁ
በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱ የህዝብ ተቃውሞዎች በጠብመንጃ ሃይል ደም እየፈሰሰ መቆሙን እንደ ድል የሚቆጠሩ አሉ። እነዚህ ክፍሎች ዜጎች በደላቸውን አስመልክቶ አስተያየት ሲሰጡ እንኳን ደስ አይላቸውም። “ልማት ላይ ነን” በሚል “ጸረ ልማት” አድርገው ይስሏቸዋል። በደሉን ትቶ ለነሱ ግንባታ እንዲያጨበጭብ ይመኛሉ። ለነሱ ስካርና ድሎት እውቅና በመስጠት በችጋርና በጠኔው እንዲመካ ይመኙለታል። በዚህ እሳቤ የተደረገው ጉዞ ጭማቂው የሚጎመዝዝ እየሆነ ነው። አማርኛ ተናጋሪዎች (አማሮች) ላይ በጅምላ የሚፈጸመውና የተፈጸመው ግፍ ቀን የሚጠብቁ እንዲበዙ አድርጓል። አማርኛ ተናጋሪ ህጻናት ላይ የተፈጸመው ከቶውንም ሊዘነጋ የሚችል ባለመሆኑ የጨለማው ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
ጋምቤላ ምስኪኖች በጅምላ ተረሽነዋል። መሬታቸውን ተነጥቀዋል። እየተነጠቁ ነው። ኦሮሚያ ቅርሷን እያጣች ነው። ህዝቡ የማንነቱ መለያና የኑሮው መሰረት የሆነውን ሃብቱን እየተነጠቀ ነው። በመቃወማቸው በርካቶች ህይወታቸውን እስር ቤት እያሳለፉ ነው። ኦጋዴን ላይ የተፈጸመ ወንጀል ቀን የሚቆጥር ነው። አፋር ችግር አለ። ይህንን ሁሉ የሚያደረጉት ደግሞ የህወሃት ሰዎች ናቸው። ሌሎቹ አገልጋይ ድርጅቶች ከመታዘዝ የዘለለ ስልጣን ስለሌላቸው ሁሉም የሚመለከተው ህወሃትን ብቻ ነው። ስለዚህ ህወሃቶች አንድ ሊሉ ይገባል። ጨለማውን ማለፍ እንዲቻል ዛሬ ነገ ሳትሉ፣ ህዝብን አድምጡ። የወደፊቱ የሚያሳሰባቸው ክፍሎች እንደሚሉት ጨለማው ሳይውጠን የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር መወሰን አለበት። በስሙ የሚነገድበት የትግራይ ህዝብም ለሌሎች ተቃውሞ ድጋፍ ሊሰጥ እንደሚገባ ብዙዎች ይወተውታሉ። ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን ኑሮው ከመቃብር በታች የሆነው ሕዝብ ብዙም የሚያጣው ነገር የለም፤ አደጋው ግን አገር የምትባለው እንዳትኖር የሚያደርስ እንደሚሆን ይነገራል፡፡ በሰሞኑ የሕዝብ ንቅናቄ 60 ያህል ንጹሃን ዜጎች ደማቸው መፍሰሱ በደርግ ላይ ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ላደረጉት እንደ ቪኦኤ (የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ) ላሉ እና ሌሎች መሰል የሚዲያ ተቋማት ለዜናነት የሚበቃ ባይሆንም ጉዳዩ በጥብቅ የሚያሳስባቸው ወገኖች ሁኔታው ከእጅ ከወጣ ለመገመት የሚያስቸግር አደገኛ ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
በሰሜን አፍሪካ ሕዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተጀምሮ በነበረበት ወቅት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በአገራችን ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ለፖለቲካ ድርጅቶች፣ ለነጻ አውጪ ግምባሮች፣ ለተማሪዎች፣ ለወጣቶች፣ ለሠራተኛውና ነጋዴው ማኅበረሰብ፣ ለሚዲያ፣ ለዳያስፖራ፣ ለምሁራን፣ … “ጥሪ! ለሥርተከል አገራዊ ለውጥ” በሚል ጥር 26፤2003 መግለጫና ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡ በተለይ “ለገዢው ፓርቲ አባላት፣ ካድሬዎች፣ ለመከላከያ፣ ለደኅንነት እና ለፖሊስ ሠራዊት” ያቀረበው ጥሪ አሁንም የሚሰራና አሁንም መሰማት ያለበት በመሆኑ ከዚህ በታች አስፍረነዋል፡-
“ህወሃት/ኢህአዴግ ባለፉት 20 (አሁን 24) ዓመታት ኢትዮጵያን በዘር ከፋፍሎ ለራሱ የሥልጣን ማራዘሚያ ሲያደርግ፤ በተለይም የትግራይ ተወላጆችን እና ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ሲጠቀም ቆይቷል፡፡ ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ቢያደርጉት የማይከፋፈልና “ነብር ዥንጉርጉርነቱን እንደማይለቅ” ፈጽሞ የማይለያይ ሕዝብ መሆኑን በተደጋጋሚ አስመስክሯል፡፡ በመሆኑም ገዢውን ፓርቲ እስካሁን በወገናዊነትም ይሁን በግል ጥቅም በመነሳሳት ስትደግፉ የነበራችሁ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመከራ እየኖረ እናንተ ለፓርቲው ባላችሁ ታማኝነት ብቻ “በነጻነት” ልትኖሩ አትችሉም፡፡ ምክንያቱም “ሁሉም ነጻ ካልወጣ ማንም ብቻውን ነጻ መሆን አይችልምና”፡፡ ስለሆነም ይህ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እናንተንም ነጻ የሚያወጣ መሆኑን በመገንዘብ ከሕዝብ ጋር የምትቆሙበትና ለትግሉ ድጋፍ የምትሰጡበት መልካም አጋጣሚ አሁን ነው፡፡ ዕርቅ ናፋቂውና መሐሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎኑ እስከቆማችሁ ድረስ ለእናንተም ነጻነት እንደሚታገል አስተውላችሁ አጋርነታችሁን በምታገኙት አጋጣሚ ሁሉ እንድትገልጹ እናሳስባለን፡፡
“ሕዝባዊው ለውጥ በቱኒሲያና በግብጽ (በወቅቱ የአረብ ጸደይ ነበር) ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት አገዛዞቹ የልዩ ጥበቃ ሠራዊታቸውን በሕዝቡ ላይ አዝምተው ነበር፡፡ ሆኖም ሠራዊቱና የልዩ ጥበቃ ኃይሉ የሰማው ለዓመታት ሲታዘዝ የነበረውን የመሪዎቹን ቃል ሳይሆን የሕዝቡን ነበር፡፡ በሕወሃት/ኢህአዴግ ትዕዛዝ የሠራዊቱ አካላት እንዲሁም የደኅንነቱ ክፍል በሕዝባችን ላይ አሳዛኝ ድርጊት ሲፈጽም መቆየቱ የማይካድ ነው፡፡ አሁንም ተመሳሳይ ድርጊት የመከላከያና የፖሊስ እንዲሁም የልዩ ጥበቃው ኃይል እንዲፈጽም ከአቶ መለስ (አሁን ሞተዋል) ትዕዛዝ ሊሰጠው ይችላል፡፡ የተሰጣችሁን ትዕዛዝ የምትፈጽሙት የኢትዮጵያ አብራክ ክፍይ በሆኑት ወገኖቻችሁ ላይ መሆኑን በማወቅ ከዳግመኛ ስህተት እንድትቆጠቡ እናሳስባለን፡፡ “ትዕዛዝ ነው የምፈጽመው” በሚል ሰንካላ ምክንያት የኢትዮጵያን እናቶች ደግማችሁ እንዳታስለቅሱ፤ ይልቁንም ከወገናችሁ ጋር በማበር የሕዝባዊው ለውጥ አካል እንድትሆኑ በጥብቅ እናሳውቃለን” የሚል ነበር፡፡
ጨለማው እየበረታ በመሄዱ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ በፊት ይህንን ተግባራዊ ማድረግ የሚጠበቀው ከህወሃት እንደሆነ በርካታዎች ይስማማሉ፡፡ ሁልጊዜ ጠብመንጃ መፍትሔ የሚያመጣ ቢመስልም ባልተገመተ ጊዜ ያልተጠበቀ የኢላማ ለውጥ ሲያደርግ በታሪክ ተስተውሏል፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
<!–
–>
The post ጨለማው በረታ!! የትግራይ ተገንጣዮች ወስኑ!! appeared first on Medrek.